ግብርናችንን ለማዘመን፤ የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና!!!

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና!!!

የዛሬዉ ርዕሴን የወሰድኩት ቡና በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ ያለዉን ከፍተኛ ሚና በማስመልከት የጂማ ቦንሳ 04 ቀበሌ ታዳጊ የኪነት ቡድን አባላት ከረጅም ዓመታት በፊት በዚያ ጣፋጭ የልጅነት ድምጻቸዉ ያዜሙልን ከነበረዉና ዘወትር በኢትዮጵያ ሬዲዮ እንሰማዉ ከነበረዉ መዝሙራቸዉ ነዉ። ባልሳሳት የመዝሙሩ ስንኝ ከዚህ በታች ያለዉ ነዉ።

“የኢኮኖሚ ዋልታ ቡና ቡና

የገቢ ምንጫችን ቡና ቡና

የህይወታችን ገንቢ ቡና ቡና

አዉታር ነው ቡናችን ቡና ቡና”

ታዲያ በዚያን ወቅት ቡና ለኢትዮጵያ 60% የሚሆነውን የዉጭ ምንዛሬ በማስገኘት በሀገሪቷ ኢኮኖሚ ግንባር ቀደም ሚና ይጫወት ነበር። ነገር ግን አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ጊዜ የቡና ድርሻ ከጠቅላላ የኤክስፖት ዉስጥ ከ30-35% የሆነዉን ብቻ ነዉ። ለምን የቡና ድርሻ በከፍተኛ ሁኔታ ቀነስ? የእገር ዉስጥ ፍጆታ ከፍተኛ ሰለሆነ ነዉን? ከዚህ በፊት ”የቡናችን ነገር እጅግ ያሳስባል” በሚለው ክፍል ሁለት ጽሑፌ ማሳየት እንደሞከርኩት በዓለም በቡና ምርታቸዉ ከታወቁት የላይኞቹ 10 ሀገራት መካከል ከፍተኛ ድርሻ ያለዉን ቡና ለሀገር ዉስጥ ፍጆታ የምታዉለዉ ሀገር ኢትዮጵያ ናት። በዚሁ መሠረት ከጠቅላላ ምርቷ 66.1 % ቱን ለሀገር ዉስጥ ፍጆታ ታዉላለች። በሌላ በኩል በዓለም በቡና ምርቷ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኮሎምቢያ ከጠቅላላ ምርቷ 2.6% ብቻ አስቀርታ የተቀረዉን ለዉጭ ሀገር ገበያ ታቀርባለች። እ.ኤ.አ. በ2016 ብቻ 2.53 ቢሊዮን ዶላር አግኝታበታለች።

ወደ ሀገራችን ስንመለስ ቡና በዉጭ ሀገር ገበያ የነበረዉን ሚና ለመረዳት እንድንችል በዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት መረጃ ላይ በመመርኮዝ ያዘጋጀሁትን ሶስተ ግራፎች ከዚህ በታች ማየት ይቻላል። ሶስቱ ግራፎች በቅድም ተከተል የሚወክሉት ሀገሪቷ እ.ኤ.አ. ከ1993 እስከ 2016 ባሉት 24 ዓመታት ውስጥ በያመቱ የላከችዉ የቡና መጠን፣ ከሽያጩ ያገኘችዉ የዉጭ ምንዛሪ መጠን እና በእያንዳንዱ ኪሎ ግራም የተከፈላት የገንዘብ መጠንን ነዉ።

ኤክስፖርት የተደረገ ቡና መጠንን በተመለከተ፤ ምንም እንኳ በተወሰኑት ዓመታት መጠነኛ መዋዥቅ ቢታይም መረጃዉ መወሰድ ከጀመረበት ዓመታት ወዲህ የቡና ኤክስፖርት መጠን ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል። እ.ኤ.አ. በ1993 ወደ ዉጭ የተላከዉ 70 ሚሊዮን ኪ.ግ. ቡና ሲሆን በ2015 ግን ወደ 234 ሚሊዮን ኪ.ግ. በማደጉ በ23 ዓመታት ዉስጥ የ234% እድገት አሳይቷል። ከፍተኛ የኤክስፖርት ማሽቆልቆል የታየዉ ለሶስት ዓመታት ሲሆን ይህም በ2001፣ 2009 እና 2011 ነዉ። በኔ ግምት የ2016 ዝቅተኛ የኤክስፖርት መጠን ሊመዘገብ የቻለው መረጃዉ ይፋ ሲደረግ የዓመቱ አጠቃላይ የኤክስፖርት መጠን አልተጠናቀቀም ይሆናል።

ከቡና ኤክስፖርት ሀገሪቷ ያገኘችዉ የዉጭ ምንዛሪን በተመለከተ፤ በመረጃዉ መሠረት በቡና የተገኘዉ የዉጭ ምንዛሪ ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል። እ.ኤ.አ. በ1993 ከነበረዉ 129 ሚሊዮን ዶላር ተነስቶ በ2015 ወደ አንድ ቢሊዮን ዶላር ሊያድግ ችሏል። ይህም የ688% ዕድገት መሆኑ ነዉ። ከላይ እንደተገለጸዉ በተወሰኑት ዓመታት ወደ ዉጭ የተላከዉ ቡና መጠን ቢያሽቆለቅልም ባንዳንድ ዓመታት ካልሆን በስተቀር የውጭ ምንዛሪ መጠን ላይ ቅናሽ አልታየም። ለምሳሌ በ2011 ወደ ዉጭ የተላከዉ ቡና በ2010 ከተላከዉ ጋር ሲወዳደር በ 52.7 ሚሊዮን ኪ.ግ. ዝቅ ብሎ ቢገኝም ያስገኘዉ መዋዕለ ንዋይ ግን በ 2011 የተገኘዉ በ 2010 ከተገኘዉ ማነስ ሲጠበቅበት በ24.8% አድጎ ተገኝቷል። ይህም ሊሆን የቻለዉ በ2011 የአንድ ኪ.ግ. ቡና ዋጋ መረጃዉ ባለበት 24 ዓመታት ሁሉ ከፍተኛዉ ሆኖ በመመዝገቡ ነዉ።

የአንድ ኪ.ግ. ቡና ዋጋን በተመለከተ፤ በሥዕሉ እንደሚታየዉ የቡና ዋጋ በኪ.ግ. ዕድገት አሳይቷል። በ 1993 አንድ ኪ.ግ. ቡና ኢትዮጵያ የሸጠችወ በ1.85 ዶላር ሲሆን በ 2016 ወደ 4.48 ዶላር ከፍ ብሏል። ቢሆንም በተወሰኑት ዓመታት በተለይ ከ2001 እስከ 2004 ባሉት አራት ዓመታት የአንድ ኪ.ግ. ቡና ከ1.50 ዶላር በላይ መዝለል አልቻለም። ነገር ግን የቡና ዋጋ ከዚህ አገግሞ እጅግ የተሻለ ደረጃ ሊደርስ ችሏል። እስካሁን በሪኮርድነት የተመዘገበዉ ዋጋ በ 2011 የተገኘዉ 5.31 ዶላር በኪ.ግ. ነው። ለዚህ ከፍ ያለ ዋጋ እንደ ምክንያት ሊጠቀስ የሚችለዉ በተጠቀሰዉ ዓመት በአቅርቦት ላይ የነበረዉ ዝቅተኝነት ነዉ። በአቅርቦት ማነስ ምክንያት የቡና ዋጋ ከፍ ሊል ስለሚችል።

ስለዚህ ኢትዮጵያ ወደ ዉጭ የምትልከዉ ቡና በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ ሳይሆን አማራጭ የዉጭ ምንዛሪ ማስገኛ በማግኘቷ ጭምር ይመስለኛል። ምንም እንኳ የተወሰነ መዋዠቅ ቢያሳይም በሥዕሉ እንደሚታየዉ የተላከዉ ቡና መጠን እየጨመረ እንጂ እየቀነሰ አልመጣም። ሰለዚህ ኢትዮጵያ ወደ ዉጭ ከምትልካቸዉ ዕቃዎች ጋር ስናወዳድር የቡና ድርሻ ቀድሞ ከነበረዉ ቀንሶ የታየዉ የሌሎች ወደ ዉጭ የሚላኩ ዕቃዎች ድርሻ በመጨመሩ ነዉ። ይህም እንደ ሰሊጥና አበባ የመሳሰሉትን ያካትታል። ለምሳሌ አንድ የዓለም አቀፍ መረጃ እንደሚያሳየዉ እ.ኤ.አ. በ2016 ኢትዮጵያ ከአበባ ሽያጭ 225 ሚሊዮን ዶላር አግኝታለች።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እንገናኝ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 2፤ 2011 ዓ.ም.

አስተያየት ያስቀምጡ