በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤
የኢትዮጵያ የስንዴ አብዮት
እንደሚታወቀዉ ሁሉ “አብዮት” የሚለዉ ቃል የሚወክለዉ በአጭር ጊዜ ዉስጥ መሠረታዊ ለዉጥ የሚያመጣ መዋቅርን ነዉ። ቢሆንም አንዳንድ ረዘም ያለ ጊዜ የወሰዱ ሂደቶችም እንደ አብዮት የተቆጠሩ ሂደቶች አሉ።
ከግብርና ጋር በተያያዘ “አብዮት” የሚል ቅጥያ ያላቸዉ በርካታ ስያሜዎች ጥቅም ላይ ዉለዋል። ጥቂቶቹን ከዚህ በታች ማየት ይቻላል።
- የመጀመሪዉ የግብርና አብዮት፣ ይህ የተከናወነዉ የሰዉ ልጅ እህል አሳድጎ መጠቀም በጀመረበት ጊዜ ሲሆን ይህም የዛሬ አሥር ሺህ ዓመት ገደማ ነበር።
- ሁለተኛዉ የግብርና አብዮት፣ ይህ የተከናወነዉ በዘመናዊ የእርሻ መሣሪዎች በመታገዝ ምርትና ምርታማነት በአዉሮፓ ያደገበት ወቅት ሲሆን ይህም ከዘሬ 100 እስከ 200 ዓመታት በፊት ነበር።
- አረንጓዴዉ አብዮት (ወይም ሶስተኛዉ የግብርና አብዮት)፣ በተለምዶ “አረንጓዴዉ አብዮት” ተብሎ የሚታወቀዉ እ.ኤ.አ. በ1960 ዎቹና 70ዎቹ የስንዴና የሩዝ ምርትን በከፍተኛ ደረጃ እንዲያድግ ያደረገበት ክስተት ነበር። ይህ ከፍትኛ የምርት እድገት ሊመጣ የቻለዉ ቁመታቸዉ አጠር ያሉና መጋሸብን ወይም መውደቅን የሚቋቋሙ ዝርያዎች በገበሬዎች ዘንድ እንዲደርሱ በመደረጉ ነዉ። በአረንጓዴዉ አብዮት ዕድሉን አግኝተዉ ምርታማነታቸዉን ማሳደግ የቻሉት በኤሲያና በደቡብ አሜሪካ የሚገኙ ገበሬዎች ሲሆኑ በአፍሪካ የነበሩት ግን የዚህ አብዮት ተጠቃሚ ሊሆኑ አልቻሉም። ምክንያቱም በአፍሪካ በብዛት የሚበቅሉት ሰብሎች አረጓዴዉ አብዮት ትኩረት የሰጠቻቸዉ ስንዴና ሩዝ ሳይሆኑ እንደ ማሽላ፤ በቆሎ፣ዳጉሣ እና ጤፍ የመሳሰሉት ናቸዉ። አረንጓዴዉ አብዮት እንዲሳካ በተለይ በስንዴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉት ዶክተር ኖርማን ቦርሎግ የተባሉና ለዚሁ ሥራቸዉ የኖብል ሽልማት ያገኙ ናቸዉ። የአረንጓዴዉ አብዮት አባትም ተብለዉ ይጠራሉ። በተመሣሣይ መልኩ በሩዝ ምርምርና ሥርፀት ከፍተኛ ዉለታ የዋሉትና የህንድ አረንጓዴ አብዮት አባት የሚባሉት ዶክተር ስዋሚናታን ናቸዉ።
- ሁሌ አረንጓዴ አብዮት፤ ይህ ስያሜ የተሰጠዉ ምርትና ምርታማናትን በዘላቂነት ለማሳደግ ተብሎ ነዉ።
- አራተኛዉ የግብርና አብዮት፣ በአቡኑ ጊዜ እየተካሄድ ያለዉን የዲጂታሊዜሽንና ፕሪሲሺን እርሻ የሚባለዉን ይወክላል።
- የአፍሪካ አረንጓዴዉ አብዮት፣ ይህን አብዮት በአፍሪካ ለማሳካትና የሰብሎችን ምርታማነት ለማሳደግ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ከፍተኛ አስተዋጾ እያደረጉ ናቸዉ። ከነዚህ ውስጥ አግራ የሚባለዉና መቀመጫዉን በናይሮቢ ያደረገዉ መንግሥታዊ ያልሆነ ደርጅት በግንባር ቀደምትነት ሊጠቀስ ይችላል።
- የቀስተ ዳመናዉ አብዮት፣ ይህ አብዮት እስካሁን ድረስ ተግባራዊ መሆኑ በትክክል ባይታወቅም ለአፍሪካ ግብርና እንደ መፍትሔ ይሆናል ተብሎ የቀረበ ነበር። ሀሳቡን ያቀርቡት ምሁራን እንደሚሉት ለአፍሪካ ግብርና መፍትሔዉ አንድ ብቻ ሳይሆን የተለያዩ እንደሆኑ ለማሳየት ነዉ። ምክንያቱም በአህጉሩ ያሉ ሰብሎች ዓይነት፣ የምርት ግብአት አጠቃቀም፣ ወዘተ የተለያየ ስለሆነ ነወ።
የኢትዮጵያ የስንዴ አብዮት፣ በቅርቡ ማለትም ሚያዚያ 12 ቀን 2011 አዲስ አበባ በሚገኘዉ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የመሰብሰቢያ አዳራሽ ውስጥ የግብርና ሚኒስትር በመስኩ ከተሰማሩ ምሁራን ጋር ዉይይት አድርጎ ነበር። በዚህ የግብርና ሚኒስትሩ አቶ ኡመር ሁሴን ባቀረቡት የመነሻ ጽሁፍና በመቀጠል በመሩት ስብሰባ ላይ እኔም ለመሳተፍ ዕድሉን አግኝቼ ነበር። በቀረበዉ ጽሁፍ በግልጽ መረዳት እንደሚቻለው ምንም እንኳ ኢትዮጵያ ስንዴን በማምረት ከአፍሪካ በሶስተኛ ደረጃ ላይ ብትገኝም (ከግብጽና ሞሮኮ ቀጥሎ) የሀገሪቱን የስንዴ ፍላጎት ማርካት አልታቻለም። ስለዚህ ሀገሪቷ በያመቱ ስንዴ ወደ ሀገር ዉስጥ ለማስገባት ከፍተኛ የዉጭ ምንዛሪ ታወጣለች። ይህንን ከዉጭ የምታስገባዉን ስንዴ በሂደት በመቀነስና ከአራት ዓመታት በኋላ (ማለትም እ.ኤ.አ. በ2023) ከነጭራሹ ለማቆም ዕቅድ ተይዟል። በዕቅዱ መሠረት ከአራት ዓመት በኋል የስንዴ ምርታማነትን በሄክታር ወደ አርባ ኩንታል ለማሳደግ ታስቧል። ከአንድ ሄክታር የሚመረተውም ይሁን በአጠቃላይ በሀገሪቱ ምርት ሊያድግ የሚችለዉ በዋናነት የመስኖ እርሻን፣ ኩት ገጠም እርሻን እና የምርት ግብአቶችን በመጠቀም እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን ለተግባርነቱም የምሁራንም ሆነ የሌሎች ባለድርሻ አካላት አስፈላጊነት ተገልጿል። በዚሁ መሠረት ምሁራንን ከሚኒስትሩ መሥሪያ ቤት ጋር የሚያገናኝ አማካሪ ቡድን እንደሚቋቋም ተውስኗል። በግብርና በኩል ከገበሬዎች ጋር በቅርበት የሚሰሩ ወደ ሰስሳ ሰባት ሺህ የሚጠጉ ባለሙያዎች በምርምር የተገኙ ዉጤቶችን ገበሬ ዘንድ እንደሚያደርሱና የድርሻቸዉን እንደሚያበረክቱ ተገልጿል። ይህ የመንግሥትን ዕቅድ በቅርቡ ከመገናኛ ብዙሀንም ሰምቻለሁ።

ማጠቃለያ
ከዚህ ቀደም “በምግብ ዋስትና ጥራትም ቢታከልበት” በሚል ርዕስ ሥር የሚከተለዉ ጽፌ ነበር። “ኢትዮጵያን ብቻ ብንመለከት የአለም የእርሻና የምግብ ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየዉ አ.ኤ.አ. በ2016 ብቻ 1.5 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት የተለያዩ የእርሻ ዉጤቶችን ወደ ሀገር ዉስጥ አስገብታለች። ከነዚህ ውስጥ ከፍተኛዉን ድርሻ የሚይዙት የፓልም ዘይት 522.7 ሚሊዮን ዶላር፣ ስንዴና የስንዴ ዉጤቶች 305.5 ሚሊዮን ዶላር፣ ስኳር 260.6 ሚሊዮን ዶላር እና ሩዝ 201.7 ሚሊዮን ዶላር ናቸዉ። ነገር ግን በተመሣሣይ ዓመት ቡና፣ ሰሊጥንና የቁም ከብቶችን ጨምሮ ወደ ውጭ ከምትልካችዉ የእርሻ ዉጤቶች ሀገሪቷ ባጠቃላይ ያገኘችዉ 2.2 ቢሊዮን ዶላር ብቻ ነዉ። ይህ የሚያሳየዉ ከሰማኒያ ፐርሰንት በላይ ህዝቧ በእርሻ ቢተዳድርም ከዚህ ሴክተር የሚገኘዉ ምርት የሀገሪቷን የምግብ ፍላጎት እንደማያሟላ ነዉ።”
ስለዚህ በግብርና ሚኒስቴር በኩል ሀገሪቱን በስንዴ ፍላጎት ራስን ለማስቻል የቀረበዉ ዕቅድ አስፈላጊና ወቅታዊም ነዉ። ለተግባሪነቱም ሁላችንም የድርሻችንን መወጣት ይኖርብናል። ሀገሪቷ በስንዴና በሌሎች የእርሻ ምርቶች (ስኳርና ዘይትን ጨምሮ) ራሷን ከቻለች ደስታችን ወሰን አይኖረዉም። ምክንያቱም ከሰማንያ ፐርሰንት በላይ የሚሆነዉ ህዝባችን በግብርና እየተዳደረ ለዜጋዉ በቂ የሆነ የምግብ እህል አለመመረቱ ያሳዝናልና ነዉ። ከዚህ በታች የራሴን ምክር ለመለገስ እወዳለሁ።
1ኛ) ሁለት ሰብል በዓመት፤ በአንዳንድ ሥፍራዎች (በተለይም በመካከለኛዉና ታችኛዉ አዋሽ) ስንዴን ለመዝራት የታቀደዉ የጥጥ እርሻን ተከትሎ በዓመት ሁለት ሰብል ለማምረት ነዉ። ይህም እንደሚቻል የተረጋገጠዉ በቅርቡ ከዚሁ አካባቢ በሰፋፊ ማሳዎች በተደረጉ ሰርቶ ማሳያዎች ነዉ። ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ በጥጥ ለቀማና የስንዴ ማሳ ዝግጅት መካከል ያለዉ ጊዜ እጅግ አነስትኛ ይሆናል። ይህ ሲያጋጥም በቂ የማሳ ዝግጅት ሳደረግበት ስንዴ ይዘራል፣ የተዘራዉ ስንዴም በአግባቡ ሊያድግ አይችልም።
2ኛ) ትክክለኛ ዝርያ በትክክለኛ ሥፍራ፤ እንደሚታወቀዉ ሁሉ እያንዳንዱ ዝርያ የራሱ የሆነ ተስማሚ የአየር ንብረትና የአፈር ሁኔታ አለዉ። ለምሳሌ ጨዋማነት፣ አሲዳማነት፣ ድርቅ፣ ወዘተ የሚያጠቃቸዉ ሥፍራዎች የሚላኩት ዝርያዎች በሚላኩበት ሥፍራ ያሉትን እክሎች የሚቋቋሙ መሆን ይገባቸዋል።
3ኛ) ከፍተኛ ጥንቃቄ ለስንዴ በሽታዎች፤ ስንዴ ለበርካታ ዓይነት በሽታዎች የተጋለጠ ስብል ነዉ። በተለይ ዋግ ለሚባል በሽታ ተጠቂ ሲሆን በቅርብ ጊዜ ጸድቅዉ የወጡ ዝርያውች እንኳ በአጭር ጊዜ በሽታዉንዉን የመቋቋም አቅም ሊያጡ ይችላሉ። ስለዚህ የስንዴ እርሻን ስናስፋፋ በስንዴ በሽታ ላይ ጥልቅ ዕውቅት ካላቸዉ ባለሙያዎች ጋር በቅርበት መሥራት ያስፈልጋል።
4ኛ) የምርት ግብአቶች በወቅቱና ለሁሉም ተደራሽ፤ የምርት ግብአቶች አስፈላጊነትና በወቅቱ ለገበሬው እንዲደርሱ ማድረግ አጠያያቂ አይደለም። ነገር ግን አንዳንድ ገበሬዎች በቂ መዋዕለ ንዋይ ላይኖራቸዉ ስለሚችል ብድር የሚያገኙበት መንገድ ቢመቻች። በተለይ ማዳበሪያና የመስኖ ዉሃን እንዴት እነስተኛ ገበሬዎች ዘንድ ሊደርስ እንድሚችል ዕቅድ ማዉጣት ያስፈልጋል። ከአርባና ሀምሳ ዓመታት በፊት በህንድ ሀገር ተግባራዊ የሆነዉ አረንጓዴዉ አብዮት ከተቸቸባቸዉ ነጥቦች ዋነኛዉ በድሃና ሀብታም ገበሬዎች መካከል ያለዉን የኢኮኖሚ ልዩነት ማስፋቱ ነዉ። ምክንያቱም ለመስኖና ሌሎች ግብአቶች ክፍያ በመፈጸም መጠቀም የቻሉት ሀብታሞቹ ገበሬዎች ብቻ ሲሆኑ ድሀዎቹ ገበሬዎች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ሊሆኑ አልቻሉም፤ ኑሮአቸዉም ብዙ መሻሻል አልታየበትም።
በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እንገናኝ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ሰኔ 1፤ 2011 ዓ.ም.