ግብርናችንን ለማዘመን፤ አንድ ሚሊዮን ፍጥረታት ሊጠፉ 2 !!!

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

አንድ ሚሊዮን ፍጥረታት ሊጠፉ!!!

ክፍል ሁለት

በክፍል አንድ ጽሁፌ እ.ኤ.አ. ሜይ 6 ቀን 2019 IPBES በሚባል ዓለም አቀፍ ድርጅት ይፋ የሆነዉን በብዝሀ ህይወት ላይ ያትኮረ ነገር ግን አስደንጋጭ የሆን ሪፖርት ባጭሩ አቅርቤ ነበር። በዛሬዉ ጽሁፌ ስለ አህጉራችን አፍሪካ በዝርዝር ከቀረቡት መካከል የተወሰኑትን ለማሳያነት አቀርባለሁ። በመጨረሻም የራሴን ማጠቃሊያ ከትቤ ጽሁፌን እደመድማለሁ።

ድርጅቱ ከላይ በተጠቀሰዉ ዕለት ለህዝብ ይፋ ያደረገዉ ሪፖርት መነሻ ያደረገዉ ጥቂት ቀደም ብሎ በድርጅቱና በአጋሮቹ በታተሙ ወደ ስምንት የሚደርሱ በጥናት ላይ የተመረኮዙ ሥራዎች ላይ ነዉ። ከስምንቱ ሥራዎች አንዱ በአፍሪካ ላይ ያተኮረ ነዉ። ይህ በአፍሪካ ላይ ያተኮረዉ ሪፖርት እንደ ሀገሮቹ ቅርበት፣ የአየር ንብረት ተመሳሳይነትና የብዝሀ ሕይወት ሁኔታ አህጉሪቷን በአምስት ዋና አካባቢዎች ከፍሎ በተለያዩ መለኪያዎች ያሳያል። እነዚህ አምስት ክፍሎች ሰሜን አፍሪካ፣ ምዕራብ አፍሪካ፣ ማዕከላዊ አፍሪካ፣ ደቡባዊ አፍሪካ እና ምሥራቅ አፍሪካና በአካባቢዉ ያሉ ደሴቶች ናቸዉ። እነደሚታወቅዉ ሀገራችን በመጨረሻ በተገለጸዉ ክፍል ውስጥ ትካተታለች። ሪፖርቱ ከዚህ በታች በተገለጹት ነጥቦች ሥር አህጉሪቷ አሁን ያለችበትን ሁኔታና የወደፊት ዕድሏን ይገመግማል። ሆኖም ግን በጽሁፌ ጥቂቶቹን ብቻ እገልጻለሁ።

አፍሪካ ያላት የተፈጥሮ ጸጋ

  • አህጉሪቷ እጅግ ከፍተኛ የሆነ ብዝሀ ሕይወት አላት
  • ከሌላዉ የዓለማችን ክፍል ሲወዳደር ከፍተኛ ቁጥር ያላቸዉ ግዙፍ አጥቢ እንስሳት የሚኖሩበት አህጉር ነዉ።እነዚህ ግዙፍ እንስሳት እንድ ጉማሬ፣ ዝሆን፣ ጎሽ እና ቀጭኔን የመሳሰሉትን ያካትታሉ።
  • ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ የአህጉሯ ህዝብ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ የዚህ ብዝሀ ሕይወት ተጠቃሚ ነዉ
  • ቢሆንም አፍሪካ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋ በአግባቡ አልተጠቀመችም
  • በአሁኑ ጊዜ በሰፊዉ በጥቅም ላይ ከዋሉት ሰብሎች መካካል እንደ ስንዴ፣ ገብስ፣ ዳጉሣ፣ ማሽላ፣ ጤፍ፣ ቡና ወዘተ መገኛቸዉ ወይም መነሻቸዉ አፍሪካ ነዉ
  • የራሴ ማስታወሻ፣ ርፖርቱ የሀገራችንን ጤፍን በተመለከተ በምግብ ዋስትና የሚኖረዉን ከፍተኛ አስተዋጾ ከመግለጹም በተጨማሪ በሥዕል የተደገፈ መረጃም አቅርቧል። ሪፖርቱ ጤፍ በዉስጡ የያዛቸዉ ለሰዉነታችን ጠቃሚ የሆኑ ንጥረ ነገሮች መጠን ያሳያል። ቢሆንም በዚህ ሪፖርት መሠረት በ100 ግራም የጤፍ ፍሬ ውስጥ ያለዉ የፕሮቲን መጠን 3.87 ግራም ብቻ እንደሆነ ቢያሳይም ከዚህ በፊት የታተሙ ጽሁፎች እንደሚያሳዩት ግን በተመሳሳይ የጤፍ ፍሬ ክብደት ውስጥያለዉ የፕሮቲን መጠን 13 ግራም እንደሆነና ይህም በስንዴ ዉስጥ ካለዉ የፕሮቲን መጠን ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ነዉ።

አፍሪካ የሚደርስባት ጫና

  • ወደ 20% የሚጠጋ ወይም 6.6 ሚሊዮን ስኩዌር ኪሎ ሜትር የሚሆን የአፍሪካ መሬት ለከፍተኛ አደጋ ተጋልጧል። ዋና ምክንያቶቹም የአፈር መሸርሸር፣ የመሬት ጨዋማነት፣ የአፈር ብክለት፣ የዛፎች መቆረጥና የአፈር ለምነት መቀነስ ናቸዉ።
  • በአሁኑ ጊዜ በአህጉሯ የሚኖረዉ 1.25 ቢሊዮን ህዝብ እ.ኤ.አ. በ2050 (ማለትም ክ31 ዓመታት በኋላ) በእጥፍ ያድጋል። በከተማ የሚኖረዉ የአህጉሯ የህዝብ ቁጥርም ከላይ በተገለጸዉ ጊዜ በሦስት እጥፍ ያድጋል ተበሎ ይጠበቃል። አስፈላጊ የሆኑ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ካልተነደፉና በተግባር ላይ ካልዋሉ በብዝሀ ሕይወትና በሌሎች ሴክተሮች ላይ ከፍተኛ የሆነ ጫና ይፈጥራል።
  • የአየር ንብረት ለውጥ በአህጉሪቱ ባሉ የተክሎችም ሆነ የእንስሳት ብዝሀ ሕይወት ላይ ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ዉጤት እንደሚያመጣ ይጠበቃል። በዚሁ መሠረት በአማካይ ወደ እስከ 25% የሚጠጋ የአህጉሯ ብዝሀ ሕይወት ለአደጋ ይጋለጣል።
በሥዕሉ እንደሚታየዉ በሆራ ሀይቅ አካባቢ (ቢሾፍቱ) በአፈር መሸርሸርና በአካባቢዉ ባለዉ ንጣፍ ድንጋይ ምክንያት አብዘኛዉ  የዛፉ ሥር ለአደጋ ተጋልጧል። ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ

አፍሪካ ያላት ተስፋ

  • የአፍሪካ ህብረት የነደፋቸዉን የተለያዩ የፖሊሲ አቅጣጫዎች ተፈጻሚ ለማድረግ የማህበሩ አባል ሀገራት  በትኩረት እየሠሩ ይገኛሉ።

ማጠቃሊያ፣ ይህ የአንድ ሚሊዮን ፍጥረቶቻችን ሊጠፉ እንደሆነ ያበሰረዉ አስደንጋጭ ዜና በመላዉ ዓለም በሚገኙ መንግሥታትና ሚዲያዎች ከፍተኛ ሽፋን አግኝቶ ነበር። በሀገራችን ያሉ ሚዲያዎች በዚህ አሳሳቢ በሆነውና በበርካታ ፍጥረቶቻችን ላይ የተጋረጠዉን አደጋ የሚገልጽ ሪፖርት ምን ያህል ትኩረት እንደሰጡትና ህብረተሰባችንም ምን ያህል ግንዛቤ እንዳገኘ ማወቅ አልቻልኩም። በርግጥ የዚህ ሪፖርት ይፋ መሆንን የኢትዮጵያ ሣይንስ አካዳሚ በድህረ ገጹ ላይ አውጥቶታል።

በብዝሀ ሕይወት እንክብካቤ የሚኖረን አመለካከትም ሆነ አስተዋጽኦ ትንሽ ከሚመስል ነገር ግን ከፍተኛ ተጽዕኖ ሊኖረዉ ከሚችል ነገር መጀመር ይኖርብናል። እንደሚታወቀዉ ላስቲክ ወይም ፌስታል በቀላሉ ወደ አፈርነትም ሆነ ወደ ሌላ ነገር ስለማይለወጥ በየብስም ሆነ በባህር ውስጥ የሚኖሩ ፍጥረታት ይመገቡታል። በብዝሀ ሕይወትም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል። በዚህ መሠረት እስካሁን ድረስ በ127 ሀገሮች ውስጥ በፌስታል አጠቃቀም ላይ ህግ ወጥቷል፡ ከአፍሪካ እስካሁን ድረስ በፌስታል ላይ ማዕቀብ ያደረጉ አገሮች 34 የደረሱ ሲሆን በቅርቡ ዕገዳዉን የተቀላቀለችዉ ታንዛኒያ ናት። ተግባራዊ ያደረገችዉም ከአምስት ቀናት በፊት እ.ኤ.አ. ከጁን 1፣ 2019 ጀምሮ ነዉ።ኬኒያ ከሁለት ዓመት በፊት ባወጣችዉ ጠንከር ያለ ህግ በግልጽ እንዳስቀመጠችዉ ከላስቲክ የተሠራ ከረጢት ያመረተም ሆነ የሸጠ እንዲሁም የተጠቀመ 1.1 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ቅጣት ወይም የአራት ዓመታት እስር ይጠብቀዋል። በታንዛኒያ ቅጣቱ ፌስታል ይዞ ለተገኘ 2,487 ብር ወይም የአንድ ሣምንት እስር ሲሆን ላስቲኩን ላመረተ ደግሞ 13.3 ሚሊዮን ብር ወይም የሁለት ዓመት እስር ነዉ። የታንዛኒያ ፕሬዘዳንትም ለህዝባቸዉ ምሳሌ ለመሆን በትላንትናዉ ዕለት በሀገራችን እንጠቅም የነበረዉን ከቃጫ የተሠራ ዘንቢል ይዘዉ ሲገበያዩ ታይተዋል። በሀገራችን የነበሩት እነዚያ ቆንጆ ዘንቢሎች ፍጥረታቶቻችንን ለማጥፋት ቆርጦ በተነሣዉ ፌስታል ከተተኩ ዓመታት ተቆጥረዋል። ይህ ብቻም ሳይሆን ፌስታሎቹ በየሥፍራዉ ወድቀዉ አካባቢያችንን ከማቆሸሽ አልፈው በቂ የግጦሽ መሬት ሳያገኙ ለሚንከራተቱት ለማዳ እንስሳዎችንም ጠንቅ እየሆኑ ነዉ። ታዲያ አብዘኛዉ የዓለም ህዝብ ሊያያቸዉ እንኳ እየተጠየፈ ባለዉ ፌስታል ላይ መቼ ነዉ እርምጃ የምንወስድበት? በማጠቃለዬ የፌስታሉ ነገር ትኩረቴን ሳበዉ እንጂ የብዝሀ ህይወት እንክብካቤና የሌሎች ተዛማች ሥራዎች የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ማሳትፍ ያለበት ሲሆን ይህም መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ይጨምራል።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እንገናኝ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ግንቦት 28፤ 2011 ዓ.ም.

አስተያየት ያስቀምጡ