ግብርናችንን ለማዘመን፤ አንድ ሚሊዮን ፍጥረታት ሊጠፉ 1 !!!

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

አንድ ሚሊዮን ፍጥረታት ሊጠፉ!!!

ክፍል አንድ

የዛሬዉ ጽሑፌ የሚያተኩረዉ ከአንድ ወር በፊት እ.ኤ.አ. ሜይ 6 ቀን 2019 IPBES በሚል ምህጻረ ቃል የሚታወቀዉና በብዝህ ሕይወትና አካባቢ ላይ የሣይንስ ፖሊሲ መድረክ ሆኖ በሚያገለግለዉ ዓለም አቅፍ ድርጅት ይፋ በሆነዉ አስደንጋጭ ሪፖርት ዙሪያ ነዉ። የዚህ ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤቱ በቦን ጀርመን ቢሆንም በተወሰኑ የዓለማችን ክፍሎች መለስተኛ ቢሮ አላቸዉ። ይህ በበቂ መረጃ ላይ ተመርኩዞ የቀረበዉ ሪፖርት የድርጅቱ አባል የሆኑ 128 ሀገራት የተወከሉቡት ሲሆን ኢትዮጵያም በብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክቴር (ዶክተር መለሰ ማርዮ) እና ምክትል ዋና ዳይሬክቴር (ዶክተር ፈለቀ ወልደየስ) ተወክላለች። ከዚህ በተጨማሪ የአፍሪካ አህጉርን በመወከል በቢሮ ደረጃ እንዲሳተፉ ከተመረጡት ሶስት ታዋቂ ግለሰቦች መካከል በመስኩ ከፍተኛ አስተዋፅዖ በማበርከት ላይ የሚገኙት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲዉ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰዉ አንዱ ናቸወ። ስለ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ከዚህ ቀደም የቡናችን ነገር እጅግ ያሳስባል በሚለዉ ክፍል አንድ ጽሑፌ በአጭሩ ገልጬ ነበር። ከዚህ በተረፈ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተዉጣጡ በመስኩ የታወቁ ባለሙያዎች በሪፖርቱ ላይ ተሳትፎ አድርገዋል።

ሪፖርቱ ለማመን የሚያስቸግሩ ነገር ግን ትክክለኛ የሆኑ መረጃዎችን አካቷል። የቀረበዉ መረጃ በርካታ ቢሆንም በዚህ አጭር ጽሑፌ የተወሰኑትን ብቻ አቅርቤአለሁ። የሪፖርቱን ሙሉ አካልና ተዛማች መረጃዎች ከዚህ ቀጥሎ ባለዉ ሊንክ ማግኘት ይቻላል https://www.ipbes.net/news/ipbes-global-assessment-preview

ይህ ጥልቅ ምርምር የተካሄደበት ሪፖርት በሚቀጥሉት ርዕሶች ሥር እስካሁን ያጋጠመዉንና ወደፊትም ሊያጋጥሙ ይችላሉ ተብሎ የሚገመቱትን በዝርዝር አቅርቧል። እነዚህም ፍጥረታት፣ ምግብና እርሻ፣ ውቅያኖስና ዓሣ፣ ጫካ፣ ማዕድን ማዉጣትና ኢነርጂ፣ የከተሞች መስፋፋትና ሶሽዮ ኢኮኖሚክስ፣ ጤናና የአየር ንብረት ለዉጥ ናቸዉ። ከዝርዝሮቹ ውስጥ ለዛሬዉ ጽሁፌ ጥቂቶቹን ከዚህ በታች አቀርባለሁ።

ከላይ በሥዕሉ የሚታየዉ በደህና ሁኔታ ተጠብቆ የሚገኘዉ የኮኒዝ ጫካ ሲሆን የሚገኘዉም በበርን ካንቶን በስዊዘርላንድ ሀገር ነዉ። ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ

ፍጥረታትን በተመለከተ

  • ባሁኑ ጊዜ ስምንት ሚሊዮን ዓይነት የተክል እና እንስሳት (ነፍሳትን ጨምሮ) በምድር ላይ ይገኛሉ
  • ከነዚህ ዉስጥ እስከ አንድ ሚሊዮን የሚገመቱት በቅርቡ ከምድር ገጽታ እንደሚጠፉ ይጠበቃል!!!
  • በየብስ ከሚኖሩት 5.9 ሚሊዮን ፍጥረታት ውስጥ ወደ 500 ሺህ የሚጠጉት በቂ መኖሪያ አይኖራቸዉም
  • በቂ ጥናት ከተደረገባቸዉ ፍጥረታት መካከል በአማካይ 25%ቱ የመጥፋት አደጋ ያጋጥማቸዋል
  • በ21 ሀገሮች በተደረገዉ ጥልቅ ጥናት መሠረት አደገኛ የሆኑና ኢንቬዚቭ ተብለዉ የሚጠሩ አረሞች ብዛት ባለፉት 50 ዓመታት ብቻ በ70% ጨምሯል

ምግብና እርሻን በተመለከተ፤

  • እ.ኤ.አ. ከ1980 እስክ 2000 ባሉት 20 ዓመታት ብቻ 100 ሚሊዮን የሚጠጋ መሬት ወደ እርሻ ተለዉጧል
  • የአደገኛ አየር ብክለት መንስኤ ተብለወ ከሚታወቁት በተለይ ለግሪን ሀዉስ ጋዝ መንስኤ ይሆናሉ ተብለው ከተለዩት ውስጥ ወደ 25% የሚጠጉት መነሻቸዉ እርሻ ነዉ

ጫካን በተመለከተ

  • ወደ 50% የሚጠጋ የእርሻ መሬት እንዲስፋፋ የተደረገዉ ጫካን በመመንጠር ነዉ
  • እ.ኤ.አ. ከ1990 እስከ 2015 ባሉት 25 ዓመታት ብቻ ወደ 290 ሚሊዮን የሚጠጋ የተፈጥሮ ደን ተመንጥሯል
  • እ.አ.ኤ. በ2017 ብቻ ዛፍን በመቁረጥ አራት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር የሆነ ጠዉላ ተመርቷል
  • ከሁለት ቢሊዮን በላይ የሆነ የዓለማችን ህዝብ ምግብ ለማብሰልም ሆነ ለሌላ አገልግሎት እንጨትን ይጠቀማል

ማዕድን ማዉጣትና ኢነርጂን በተመለከተ

  • ምንም እንኳ ከአንድ ፐርሰንት በታች የሆነ የዓለማችን መሬት ለማዕድን አገልግሎት ቢዉልም ይህ ሴክተር በብዝሀ ሕይወት፤ በአየር ብክለት፣ በዉሃ ጥራት እና በሰዉ ጤና ላይ ከፍተኛ አሉታዊ ጎን አለዉ
  • በዓለም ወደ 17 ሺህ የሚጠጉና በ171 ሀገራት ያሉ ትላልቅ የማዕድን የቁፋሮ ሥፍራዎች ይገኛሉ

ጤናን በተመለከተ

  • በያመቱ ከ300 እስከ 400 ሚሊዮን ቶን የሚሆን ከፋብሪካዎች የሚወጣ መርዛማም ሆነ ሌላ ዓይነት ቆሻሻ ሳይታከም ወደ ወንዝ ወይም ሌላ የዉሃ አካል እንዲደባልቅ ይደረጋል
  • ወደ 40% የሚሆን የዓለማችን ህዝብ ንፁህ የመጠጥ ዉሃ አያገኝም
  • ባለፉት 40 ዓመታት ፕላስቲክን በመጠቀም የደረሰዉ ብክለት በአሥር እጅ አድጓል

የአየር ንብረት ለዉጥ በተመለከተ፤

  • የዓለማችን አማካይ የአየር ሙቅት ከፍ ብሎ ታይቷል
  • የአየር ምቀቱ በ2 ሴንቲ ግሬድ ሲያድግ 5% የሚሆኑ ፍጥረታት ለአደጋ ይጋለጣሉ፤ ሙቀቱ በ4.3 ሴንቲ ግሬድ ከጨመረ ደግሞ ወደ 16% የሚጠጉ ፍጥረታት ከነጭራሹ ከዓለማችን ሊጠፉ ይችላሉ
  • ባለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት ብቻ የባህር ወለል በያመቱ የሶስት ሚሊ ሜትር ከፍታ አስመዝግቧል
  • እ.ኤ.አ. ከ1980 ጀምሮ ባሉት 40 ዓመታት ብቻ የግሪ ሀዉስ ጋስ ብክለት በእጥፍ አድጓል

በክፍል ሁለት ጽሑፌ በሪፖርቱ አህጉራችንን በተመለከተ የተዘገበዉንና የራሴንም ማጠቃለያ አቀርባለሁ።

እስከዚያዉ በቸር ይግጠመን።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ግንቦት 27፤ 2011 ዓ.ም.

አስተያየት ያስቀምጡ