ግብርናችንን ለማዘመን፤ ዕንቁ ዝርያዎቻችንን ለመጪዉ ትዉልድ 2

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

ዕንቁ ዝርያዎቻችንን ለመጪዉ ትዉልድ

ክፍል ሁለት

በክፍል አንድ ስለ ብዝሀ ሕይወት ጥቅምና እነርሱን ለመጪዉ ትዉልድ ለማቆየት ኢትዮጵያን ጨምሮ ባንዳንድ ሀገራት በመደረግ ላይ ያሉ ተሞክሮዎችን ገልጬ ነበር። በዛሬዉ ጽሁፌ ደግሞ በዓለም የሚገኙ የተክሎች ብዝሀ ሕይወት ጥራታቸው ሳይቀንስ ለበርካታ ዓመታት ሊጠበቁ ይቻላል ተብሎ ሰለታመነበት የስቫልባርድ ጥብቅ የዘር ባንክ (Svalbard Seed Vault) ለመግለጽ እወዳለሁ።

አንባቢያን በቀላሉ እንዲረዱ የዛሬዉ መጣጥፌን በጥያቄና መልስ መልክ አቀርባለሁ።

የስቫልባርድ የዘር ማከማቻ የት ይገኛል? የስቫልባርድ የዘር ማከማቻ የሚገኘዉ በኖርዌ ግዛት ሥር ቢሆንም ከሀገሪቷ መዲና ከሆነችዉ ከኖርዌ እጅግ ርቆ በአንድ ደሴት ላይ ይገኛል። የቦታዉ ቅርበትም ለሰሜን ዋልታ ሲሆን ለዚያ ያለዉ ርቀትም አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ያህል ብቻ ነዉ።

የዓለማችንን ምርጥ ዘሮች ለማስቀመጥ ስቫልባርድ ለምን ተመረጠ? ይህ ሥፍራ በዓለም አቀፍ ደረጃ የዘር ባንክ ሆኖ የተመረጠበት በርካታ በጎ ጐኖች ቢኖሩትም የሚከተሉት ግን በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ። 1ኛ) ቦታው ፐርማፍሮስት የተባለ በተፈጥሮ ዓመቱን በሙሉ እጅግ ቀዝቃዛ የሆነ ሥፍራ ሲሆን 120 ሜትር በተራራ ሥር ተቆፍሮ የተዘጋጀና ያለተጨማሪ ማቀዝቀዣ ዘርን ለረጅም ጊዜ ማስቀመጥ በመቻሉ፤ 2ኛ) ቦታው ሰዉ ሰራሽ ከሆኑ አዳጋዎች እጅግ የራቀ በመሆኑ፤ 3ኛ) በአካባቢዉ የሚሊታሪ እንቅስቃሴ እንዳይደረግ እገዳ የተጣለበት በመሆኑ፤ 4ኛ) በአካባቢዉ የተረጋጋ የፖለቲካ ሁኔታ መኖሩ እና 5ኛ) አካባቢዉ ከመሬት መንቀጥቀጥና ከመሳሰሉት የጂኦሎጂ እቅሰቃሴዎች የራቀ በመሆኑና የሬዴሽን መጠኑም አነስትኛ በመሆኑ ናቸዉ።

ከአንድ መቶ ሜትር በላይ በተራራ ዉስጥ ተቆፍሮ የተሰራዉና በዓለም ትልቁና ቀዝቃዛዉ የስቫልባርድ ጂን ባንክ የዉጭ ዕይታ ይህንን ይመስላል።

የስቫልባርድ የዘር ማከማቻ መቼ ሥራዉን ጀመረ? ይህ የዘር ባንክ ተመርቆ ሥራውን የጀመረዉ እ.ኤ.አ. ፌብሪዋሪ 26 በ2008 ነበር። በተመረቀበት ወቅትም ሁለት መቶ ሺህ ዓይነት ዝርያዎችን ለመቀበል ችሏል።

የስቫልባርድ የዘር ማከማቻ ስፋት ምን ያህል ነዉ? ሶስት ትልልቅ የዘር ማስቀመጫ ክፍሎች ዘንድ የሚደረሰዉ 145 ሜትር የሆነ ተራራ ሥር የተቆፈረ ዋሻ ከታለፈ በኋላ ነዉ። የእያንዳንዱ የዘር ማስቀመጫ ክፍል ርዝመት 27 ሜትር፣ ጎኑ 10 ሜትር እና የጣራዉ ከፍታ 6 ሜትር ነዉ።

በዘር ባንኩ ዘሮች በምን ዓይነት ሙቀት እንዲቀመጡ ይደረጋል? እያንዳንዱ የዘር ዓይነት በታሽገ ዕቃ ዉስጥ ከተደረገ በኋላ ሙቀቱ ከዜሮ በታች 18 ሴንቲ ግሬድ በሆነ ክፍል ዉስጥ እንዲቀመጥ ይደረጋል።

የስቫልባርድ የዘር ማከማቻ ምን ያህል ዘር ሊያስቀምጥ ይችላል? ይህ የዘር ባንክ በአለማችን ትልቁ ሲሆን 4.5 ሚሊዮን በባር ኮድ የተዘጋጁ የዘር ዓይነቶች በተገቢዉ መልክ እንዲያስቀምጥ ተደርጎ የተሠራ ነዉ። ከእያንዳንዱ የዘር ዓይነት 500 ፍሬ የሚያስቀምጥ ሲሆን በድምሩ 2.25 ቢሊዮን ፍሬ ማስቀመጥ ይችላል።

እስካሁን ምን ያህል ዘር በስቫልባርድ የዘር ማከማቻ ተቀምጧል? እስካሁን ድረስ ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ የዘር ዓይነቶች ተከማችተዉ ይገኛሉ።

ዘሮቻቸዉን በማስቀመጥ እነማን ተሳትፈዋል? እስካሁን ድረስ 76 ሀገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ዘሮቻቸዉን ወደዚህ የዘር ባንክ በመላክ እንዲቀመጥላቸዉ አድርገዋል። ከታች በስዕሉ እንደሚታዉ በዓለም አቀፍ የእርሻ ምርምር ማዕከላት ሥር የታቀፉት 11 ድርጅቶች ከፍተኛ የሆነዉን የብዝሀ ሕይወት በማበርከት የቀዳሚነቱን ቦታ ይዘዋል። እነዚህ 11 ድርጅቶች ለጅን ባንኩ ያስረከቡት የዘር ዓይነት በኃላፊነት ከሚሰሩባቸዉ ሰብሎች ጋር የተያያዙ ናቸዉ። ለምሳሌ እያንዳንዳቸዉ ከመቶ ሺህ በላይ የዘር ዓይነቶች ለጂን ባንኩ የላኩትን ብናይ CIMMYT የሚባል ድርጅት 158 ሺህ የስንዴና የበቆሎ ዝርያዎችን በመላክ የቅድሚያዉን ሥፍራ ሲይዝ፣ IRRI የሚባል ድርጅት 125 ሺህ የሩዝ ዝርያዎችንና ICRISAT የሚባል ድርጅት ደግሞ 111 ሺህ የሚደርሱ የአምስት ዓይነት ዝርያዎችን በመላክ ተከታዩን ሥፍራ ይዘዋል። የሀገራትን አስተዋጽኦ ከተመለከትን ደግሞ 120 ሺህ ዝርያዎችን በመላክ አሜርካ ስትመራ ተከታዩን ሥፍራ ጀርመን፣ አዉስትራሊያና ካናዳ ይዘዋል።

ከተለያዩ ዓለም አቀፍም ሆነ ብሔራዊ ድርጅቶች በአደራ እንዲቀመጡ ወደ ታዋቂዉ የስቫልባርድ የዘር ማስቀመጫ ባንክ የተላኩ ዝርያዎች ብዛት። ጥሬ መረጃዉ ከዚህ ቀጥሎ ካለዉ ዌብሳየት የተገኘ ሲሆን ለዚህ መጣጥፍ በሚያመች መልኩ በጸሐፊዉ ተቀነባብሯል https://www.seedvault.no

ዘሮቻቸዉን ወደ ባንክ በመላክ የአፍሪካ ተሳትፎ ምን ይመስላል? በግልጽ እንደሚታየዉ የአፍሪካ ተሳትፎ እጅግ አነስተኛ ነዉ። ሳዴክ በሚባል መጠሪያ የሚታወቁት በደቡባዊ አፍሪካ አካባቢ ያሉ አገሮች በሦስት ዙር ከላኩት 4086፣ ኬንያ በሁለት ዙር ከላከችዉ 1314፣ ናይጄሪያ በሁለት ዙር ከላከችዉ 800 እና ኡጋንዳ በሁለት ዙር ከላከችዉ 777 ዓይነት ዝርያዎች በስተቀር ኢትዮጵያን ጨምሮ የሌላ አፍሪካ ሀገር ተሳትፎ አይታይም። የብዝሀ ሕይወቷን ባለመስነካት የምትታወቀዉ ብራዚል እንኳ ካላት የብዝሀ ሕይወት ጋር ተመጣጣኝ ባይሆንም 1319 ዓይነት ዝርያዎቿን ለዚህ ግዙፍና ዘመናዊ የዘር ባንክ አበርክታለች።

ዘሮቻቸዉን በስቫልባርድ ያስቀመጡ በሚፈልጉበት ወቅት መልሰዉ መውሰድ ይችላሉን? የዚህ ታላቅ የዘር ባንክ ዓይነተኛ ባህርይ ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች የተሰባሰቡ ምርጥ ዝርያዎችን እጅግ ቀዝቃዛ በሆነ ሥፍራ በማስቀመጥ የዘሮቹን ዕድሜ ማራዘም ብቻ ሳይሆን አስቀማጮቹ ዘሮቻቸዉን በፈለጉበት ወቅት መልሰዉ መዉሰድ መቻላቸዉ ነዉ። ለዚሁም እንደ ምሳሌ ሊጠቀስ የሚችለዉ ኢካርዳ በሚባል ስያሜ የሚታወቀዉንና ዝናም አጠር በሆኑ የዓለማችን ክፍሎች በምርምርና ልማት ላይ የሚሳተፍ ድርጅትን ነወ። ይህ ዓለም አቀፍ ድርጅት ከስምንት ዓመታት በፊት በሶሪያ ጦርነት ሳይቀሰቀስ ዋና መሥራያ ቤቱም ሆነ የዘር ባንኩ ይገኙ የነበሩት አሌፖ በምትባል የሀገሪቷ ትልቅ ከተማ ዉስጥ ነበር። ሆኖም አሌፖ አንዷ የጦርነቱ ማዕከል ስለነበረች ኢካርዳ ሀገሪቱን ለቆ ለመዉጣት በቅቷል። ሆኖም ጦርነቱ ከመከሰቱ ቀደም ብሎ ኢካርዳ ያለዉን የዘር ባንክ ወደ ስቫልባርድ ጂን ባንክ ሰለላከ ዘሮቹ ከአደጋ ሊተርፉ ችለዋል። ኢካርዳም ከደረሰበት አደጋ አገግሞና የምርምር ሥፍራዎቹን በቱርክ፣ ሞሮኮና ኢትዮጵያ ባስቀጠለበት ወቅት ከዚህ ቀደም በስቫልባርድ ያስቀመጠዉን ዘር በማስመጣት የምርምር ሥራዉ እንዳይስተጓጓል አድርጓል።

ማጠቃለያ፣ ለወደፊቱ ትውልድ ጠቃሚ የሚሆን የብዝሀ ህይወትን በጥንቃቄ አስጠብቆ በማስተላፍ ካለዉ ድርሻ አንፃር አንዳንዶች የስቫልባርድ የዘር ባንክን ከኖህ መርከብ ጋር ያመሳስሉታል። ምንም እንኳ በርካታ ሀገራትና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ምርጥ ዝርያዎቻቸዉን በዚህ በዓለም ቀዝቃዛው የጂን ባንክ እንዲጠበቅላቸዉ ቢያደርጉም የአህጉራችን ተሳትፎ እጅግ አነስተኛ ነዉ፤ የሀገራችንማ ከነጭራሹ የለም። ዕንቁ ዝርያዎቻችንን ለመጪዉ ትዉልድ ለማስተላለፍ ያለንን ብዝህ ሕይወት በዚህ በተመሰከረት የዘር ባንክ ማስቀመጥ የለብንም ትላላችሁን? በኔ እምነት በዚህ ባንክ ዘሮቻችንን ብናስቀምጥ እናተርፋለን እንጂ አንከስርም። ይህንን ተግባራዊ ካደረግን ዕንቁ ዝርያዎቻችን በተፈጥሮም ሆነ ሰዉ ሰራሽ ምክንያት ሊደርሱ የሚችሉ አደጋዎችን ተሻግረዉ ለወደፊቱ ትዉልድ ሊደርሱ ይችላሉ። ስለዚህ ለተግባርነቱ ከአሁኑ መንቀሳቅስ አለብን እላለሁ።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እንገናኝ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ግንቦት 25፤ 2011 ዓ.ም.

አስተያየት ያስቀምጡ