በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤
ዕንቁ ዝርያዎቻችንን ለመጪዉ ትዉልድ
ክፍል አንድ
በአሁኑ ወቅት 250 የሰብሎች ዓይነቶች በጥቅም ላይ ይዉላሉ። ቢሆንም ግማሹን የዓለም ሕዝብ የምግብ ኮታ የሚሸፍኑት አራት ሰብሎች ብቻ ናቸዉ። እነርሱም ስንዴ፣ በቆሎ፣ ሩዝ እና ድንች ናቸዉ። ቢሆንም በመልማት ባሉ ሀገሮች በሰፊዉ በጥቅም ላይ የዋሉ እንደ ማሽላ፣ ዳጉሣ፣ ካሳቫ፣ ጤፍ፣ ወ.ዘ.ተ. ሚናም መዘንጋት የለብንም።
የብዝሀ ሕይወት ወይም ባዮዳይቨርሲቲ መኖር ለአንድ ሀገር ከፍተኛ ጥቅም ይሰጣል። ከጥቅሞቹም ዉስጥ ለምግብ ዋስትና በተለይም በቂና ጠቃሚ ንጥረ ነገር ያለው ምግብ እንዲኖር ማስቻል ነዉ። ከዚህ በተጨማሪ ብዝሀ ሕይወት በአየር ንብረት ለውጥም ሆነ በሌላ ምክንያት ሊከሰቱ የሚችሉ የሰብሎቻችንን ዕድገትም ሆነ ምርታማነት የሚፈታተኑትን ማነቆዎች እንድንጋፈጥ ያስችለናል። እነዚህ የምርት ማነቆዎችም በዝናም እጥረት የሚመጣ ድርቅን እና በተለያዩ ነፍሳት የሚከሰቱ በሽታውን ያካትታሉ። በዚህ መሠረት የአንድ ሰብል ዓይነትን ብቻ ብንወስድ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ብዝሀ ሕይወት ቢኖረዉ ባንድ አጋጣሚ የሚከሰት የምርት ማነቆን (ለምሳሌ በሽታ፣ ተባይ፣ ድርቅ) የሚቋቋም ዝርያ የማግኘት ዕድላችን ከፍተኛ ነዉ።
በሌላ በኩል የብዝሀ ሕይወት መመናመን ወይም ባንዳንድ ሥፍራዎች ከነጭራሹ መጥፋት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ለማስረጃ ያህል ባለፉት አንድ መቶ ዓመታት በተለያዩ ምክንያቶች የጠፉትን የሰብል ዝርያዎች ከዚህ በታች ማየት ይቻላል።
- ከዓለም በአማካይ 75% የሰብል ዝርያዎች፣
- ከቻይና ወደ 90% የሚጠጉ የሩዝ ዝርያዎች፣
- ከሜክሲኮ ወደ 80% የሚጠጉ የበቆሎ ዝርያዎች፣
- ከህንድ ወደ 90% የሚጠጉ የሩዝ ዝርያዎች፣
- ከአሜሪካ ወደ 90% የሚጠጉ የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎች ናቸዉ።
እዚህ ላይ ‘’ዝርያ’’ የሚለዉን ቃል የተጠቀምኩት ለረጅም ጊዜ ምርምር ከተደረገባቸዉ በኋላ በገበሬ ማሣ እንዲዘሩ ከመንግሥት ፍቃድ የተሰጣቸዉን ዝርያዎች ሳይሆን በተፈጥሮ የሚበቅሉትንና በእንግሊዘኛዉ አጠራር accession ብለን የምንጠራዉን ለማመልከት ነዉ።
በዓለም ላይ በከፍተኛ ደረጃ ያሽቆለቆለዉን የብዝሀ ሕይወት ለመታደግና ይህ መጥፎ ክስተት ወደፊት እንዳያጋጥም እያንዳንዱ ሀገር በሀገሩ የሚገኙትን የተለያዩ ዓይነት ተክሎች፣ እንስሳት እና የሌሎች ብዝሀ ሕይወት እንዲጠበቅ የራሳቸዉን ጥረት እያደረጉ ይገኛሉ። እነዚህ ከተለያዩ ሥፍራዎች ተሰብስበዉ ባንድ ሥፍራ ለረጅም ጊዜ የሚቀመጡት ናሙናዎች በተወሰነላቸዉ የሙቀትና የአየር ርጥበት መሆን ይገባል። ለምሳሌ የዘር ናሙና ከሆነ የሙቀት መጠኑ ከዜሮ ሴንቲ ግሬድ በታችና የአየር ርጥበቱም እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ክፍል ወይም ማስቀመጫ መሆን ይገባል። ይህ የተወሰነ የአየር ሙቀትና ርጥበት ሳያቋርጥ ተግባራዊ መሆን ይገባዋል። ያለበለዚያ የናሙናዎቹ ተመልሰዉ የመብቀል ሁኔታ አዳጋች ይሆናል፤ ረዥም ጊዜ የተለፋበት ሥራም ከንቱ ይሆናል።
ይህ እንዳይከሰት እያንዳንዱ ሀገር መጀመሪያ ናሙናዎችን በማሰባሰብ ከዚያም ከላይ በተገለጹት ተስማሚ ሥፍራዎች እንዲቀመጡ ያደርጋሉ። በዚህ ሁኔታ ናሙናዎቻችንን ረዘም ላለ ጊዜ የምናስቀምጥበት ሥፍራ ጂን ባንክ ይባላል። ከተወሰኑ ዓመታት በኋላም የዘሮቹ የመብቅል ችሎታ እንዳይዳከም ወይም ከነጭራሹ እንዳይጠፋ በመስክ ላይ በመዝራትና የተሰበሰበዉን አዲስ ዘር ወደ ጂን ባንክ እንደገና በመመለስ ለተጨማሪ ዓመታት እንዲቆዩ ያደርጓቸዋል።
ባሁኑ ጊዜ በዓለማችን ወደ 100 በሚጠጉ ሀገራት ወደ 1400 የሚጠጉ ጂን ባንኮች ይኖራሉ። እነዚሀም በአጠቃላይ ወደ 6.5 ሚሊዮን የሚጠጉ የተለያዩ ዝርያዎች ወይም አክሴሽኖች የያዙ ናቸዉ። በጂን ባንክ የሚቀመጥ እያንዳንዱ ናሙና የራሱ የሆነ መገለጫ እንዲኖረዉ አስፈላጊ ከሆኑ መረጃዎች ጋር አብሮ ይዘጋጃል። እነዚህ መረጃዎችም የፓስፖርት ዳታ ሲባሉ በዉስጣቸዉ ከሚያካትቱት ውስጥ ናሙናዉ ከየት እንደተገኘ ወይም እንድተሰበሰበ (የቦታዉን ትክክለኛ ሥፍራ) እና መቼ እንደተሰበሰበ ይገኝበታል።
በኢትዮጵያ ይህንን ሥራ በበላይነት የሚያስተባብረው እ.ኤ.አ. ብ1976 የተመሠረተዉና ስሙንና መዋቅሩን ከሶስት ጊዜ ያላነሰ የቀያየረዉና በአሁኑ መጠሪያዉ የኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት በመባል የሚታወቀዉ መንግስታዊ የሆነ ድርጅት ነዉ። ኢንስቲትዩቱ በተክሎች፣ በእንስሳት እና በጥቃቅን ነፍሳት ብዝሀ ሕይወት ላይ የሚሠራ ሲሆን ከተክሎች ደግሞ ለሰዉም ሆነ ለእንስሳት ምግብነት በሚያገለግሉና ለመድኃኒትም በሚዉሉ ተክሎች ላይ ትኩረት ያደርጋል። የኢንስቲትዩቱ መረጃ እንደሚያሳየዉ የተሟላ የፓስፖርት መረጃ ያላቸዉ 64 ሺህ ዓይነት ናሙናዎች በጂን ባንኩ በደህና ሁኔታ ተጠብቀዉ ይገኛሉ። ኢንስቲትዩቱ በአዲስ አበባ ካለው ትልቁ የጂን ባንክ በተጨማሪ በመቱ፣ ሀዋሳ፣ ሀረር፣ መቀሌ፣ ጎባ፣ ባህር ዳር እና አሶሳ የብዝሀ ሕይወት ማዕከላት አሉት። ከዚህ በተጨማሪ በፍቼ ሁለተኛዉ ወይም ዱፕሊኬት ጂን ባንክ የሚለዉን ያስተዳድራል። ይህ ዱፕሊኬት ጂን ባንክ የሚያገለግለው ባጋጣሚ በዋናዉ ጂን ባንክ ላይ መጥፎ ክስተት ቢያጋጥም ለመጠባበቂያነት እንዲያገለግል ተብሎ የታለመ ይመስለኛል። በዚሁ አጋጣሚ መግለጽ የሚያስፈልገዉ በዓለም ካሉ ወደ ስምንት ከሚጠጉ የአሁኖቹ ሰብሎች ከተገኙባቸዉ አካባቢዎች አንዷ ኢትዮጵያ መሆኗ ነዉ። በዚህ ‘’ኢትዮጵያ’’ ተብሎ በተሰየመዉ አካባቢ ከተገኙ ሰብሎች ዉስጥ ጤፍ፣ ቡና፣ እንሰት እና ኑግ በቀደምትነት ይጠቀሳሉ።

በኢትዮጵያ ከሚገኙ የጤፍ ብዝሀ ሕይወት መካከል የተወሰኑት በሆለታ እርሻ ምርምር ማዕከል አድገዉ ይታያሉ። ፎቶ፣ ዘሪሁን ታደለ
ከዚህ ከተገለጸዉ ዉጭ የተለያዩ ዓይነት ተክሎችን ብዝሀ ዘር በመስክ ላይም እንዲጠበቁ ይደረጋል። በዚሁ መሠረት እያንዳንዱ ሀገር የራሱ የሆኑ ብርቅዬና ለአደጋ ሊጋለጡ የደረሱትን ጭምር የሚያሳድጉበትና ለወደፊቱ የሚያቆዩበት ጋርደኖች ወካይ በሆኑ የሀገሪቱ ከፍሎች አለዉ። አንዳንዶቹ ጋርደኖች ደግሞ ከሀገራቸዉም አልፈዉ በሌላዉ ዓለምም ያሉ የተክል አይነቶችንም በመንከባከብ ለጎብኚዎች ያስተዋዉቃሉ። ከነዚህ ዉስጥ በዓለም ዝናን ካተረፉት መካከል በሪዮ ዴ ጃኔሮ ብራዚል የሚገኘዉ የጃርዲም ጋርደን፣ በኒዉዮርክ የሚገኘዉ የብሩክልን ጋርደን፣ በለንደን የሚገኘዉ የኪዉ ጋርደን፤ በሲንጋፖር የሚገኘዉና እና በስድኒ አዉስትራሊያ የሚገኘዉ የሮያል ጋርደን ሊጠቀሱ ይችላሉ።
በዓለም ያሉ የዕፅዋት ጋርደኖችን የሚያስተባብር BGCI የሚባል ድርጅት እ.ኤ.አ. በ1987 ተመስርቶ መጠነ ሰፊ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛል። በዚሁ ድርጅት አባልነት የታቀፉ በርካታ ጋርደኖች ሲኖሩ ከአፍሪካ በኡጋንዳ የሚገኘዉ የኢንቴቤ ጋርደን፣ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘዉ የኪርስቴን ቦሽ ጋርደን ሲሆኑ ከኢትዮጵያ ደግሞ በቅርቡ ተመርቆ የተከፈተዉ የአዲስ አበባዉ የጉለሌ ጋርደን እና በኢትዮጵያ ብዝሀ ሕይወት ኢንስቲትዩት ሥር የሚተዳደሩት የጂማዉና የሻሸመኔው ጋርደኖች ይገኛሉ።
በክፍል ሁለት ጽሑፌ በብዝሀ ህይወት ላይ የተደቀኑትን መጥፎ ክስተቶች በዘላቂነት ለመታደግ የመፍትሔ ሀሃብ ተብሎ በዓለም አቀፍ ደረጃ የቀረበዉንና ባሁኑ ወቅት የሚገኝበትን ሁኔታ ለማሳየት እሞክራሉሁ። እስከዚያው በቸር ይግጠመን።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ግንቦት 24፤ 2011 ዓ.ም.