ግብርናችንን ለማዘመን፤ የቡናችን ነገር እጅግ ያሳስባል 2

በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤

የቡናችን ነገር እጅግ ያሳስባል

ክፍል ሁለት

የዓለም የእርሻና የምግብ ድርጅት መረጃ እንደሚያሳየዉ እ.ኤ.አ. በ2017 በአጠቃላይ በዓለማችን የተመረተዉ ቡና 155.4 ሚሊዮን ከረጢት ወይም ጆኒያ ነበር። በኩንታል ፋንታ ከረጢት ወይም ጆኒያ የሚለዉን ቃል የተጠቀምኩበት ምክንያት ቡና ባብዘኛው ገበያ ላይ የሚቀርበዉ 60 ኪ.ግ. በሚመዝኑ መያዣዎች ሲሆን ኩንታል የሚለዉ ቃል ደግሞ 100 ኪ.ግ. የሚመዝን ዕቃን ለመግለጽ ስለምንጠቀምበት ነዉ። ከላይ በተጠቀሰዉ ዓመት ቡናን በከፍተኛ ደረጃ በማምረት የታወቁት የላይኞቹ 10 ሀገራትና ያላቸዉ ድርሻ (በአጠቃላይ በዓለም ከሚመረተው ሲነጻጸር) የሚከተሉት ናቸዉ። 1ኛ) ብራዚል 28.7%፣ 2ኛ) ቬትናም 16.5%፣ 3ኛ) ኮሎምቢያ 8.1%፣ 4ኛ) ኢንዶኔሺያ 7.2%፣ 5ኛ) ሆንዱራስ 5.1%፣ 6ኛ) ኢትዮጵያ 5.1%፣ 7ኛ) ፔሩ 3.7%፣ 8ኛ) ህንድ 3.3%፣ 9ኛ) ጉቴማላ 2.6% እና 10ኛ) ኡጋንዳ 2.2%። በግልጽ እንደሚታየዉ በዓለም ከሚመረትዉ ቡና 45.2% የሚሆነዉ በብራዚልና እና በቬትናም መሆኑ ነዉ። ከሁሉ የሚያስገርመዉ በአሁኑ ውቅት በሁለተኛ ደረጃ የምትገኘዉ ቬትናም ወደ ቡና ማምረት ቢዝነስ የገባችዉ ባለፉት 25 ዓመታት ብቻ መሆኑ ነዉ። እዚህ ላይ መታየት የሚገባዉ እነዚህ ሀገራት ቡናን ማምረት ብቻ ሳይሆን ከሚያመርቱት ቡና ምን ያህሉን ኤክስፖርት በማድረግ የውጭ ምንዛሪ እንደሚያገኙ ነዉ። እነዚህን ከፍተኛ የቡና አምራች ሀገሮችን በዚህ መሥፈርት ብናያቸዉ የሚከተለዉን እናገኛለን። ብራዚል 68.0%፣ ቬትናም 90.8%፣ ኮሎምቢያ 97.4%፣ ኢንዶኔሺያ 61.7%፣ ሆንዱራስ 65.2%፣ ኢትዮጵያ 33.9%፣ ፔሩ 69.1%፣ ህንድ 80.3%፣ ጉቴማላ 73.4% እና ኡጋንዳ 78.5% የሆነዉን የአጠቃላይ ምርታቸዉን ወደ ውጭ ገበያ ይልካሉ፤ የዉጭ ምንዛሪም ያገኙበታል። በግልጽ እንደሚታየዉ ከቡና ምርቷ እጅግ ዝቅተኛ የሆነዉን ድርሻ ወደ ውጭ ሀገር የምትልከዉ ኢትዮጵያ ናት። ይህም ሊሆን የቻለዉ የሀገር ዉስጥ ፍጆታ ከፍተኛ በመሆኑ ነዉ። ምንም እንኳ ኢትዮጵያ በቡና ምርት በዓለም በ6ኛ ደረጃ ላይ ብትገኝም ከላይ በተጠቀሰዉ ዓመት ወደ ውጭ የላከችዉ ቡና መጠን ግን በ10ኛ ደረጃ ካለችዉ ከኡጋንዳም በታች ነበር። ያም ቢሆን ከ30 እስከ 35% የሚሆነዉን የዉጭ ምንዛሪ በማስገኘት ቡና ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ ድርሻ ያበረክታል።

እዚህ በሥዕሉ እንደሚታየዉ ‘’ኢትዮጵያ’’ የሚል ሥያሜ ተጽፎበት በታዋቂዉ የቡና ሻጭ ድርጅት በዉጭዉ ዓለም ለሽያጭ ቀርቧል። በፓኮው ላይ ደግሞ ቡናዉ አረቢካ ከሚባለው የቡና የተገኘ መሆኑንና በኢትዮጵያ ያሉ ቡና አብቃዮች ረዥም ጊዜ ወስደዉ ያደረቁት እንደሆነ ከመገለጹም በተጨማሪ የቡናዉ ጣዕም ከፍተኛ እንደሆነ ተገልጿል።

በክፍል አንድ ጽሑፌ በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት በቡናችን ላይ በአሁኑ ወቅት ያጋጠመዉንና ወደፊትም ያጋጥመዋል ተብሎ የሚጠበቀዉን መጥፎ ክስተት ገልጬ ነበር። የጽሑፌ መነሻም የነበረዉ በዘርፉ በታወቁ ተመራማሪዎች በተደረጉ መጠነ ሠፊ ጥናቶችና በቅርብ ጊዜ ለህትመት በበቁ ሁለት ጽሑፎች ሲሆን እነርሱም Coffee Farming and Climate Change in Ethiopia እና Resilience potential of the Ethiopian coffee sector under climate change የሚባሉት ናቸዉ። በዛሬዉ ጽሑፌ ደግሞ ይህንን መጥፎ ክስተት ለመታደግ የመፍትሔ ሀሳብ ሊሆኑ ይችላሉ የተባሉትን አቀርባለሁ።

የመፍትሔ ሀሳብ ተብለዉ በጸሐፊያኑ የቀረቡት 12 ቢሆኑም ክዚህ በታች የተወሰኑትን በጭሩ አቀርባለሁ። ዝርዝሩን በታተሙት ጽሑፎች ማግኘት ይቻላል።

1ኛ) ወቅታዊ፣ትክክለኛና በሳይንስ የተደገፈ ዉሣኔ እንዲኖር ማድረግ፤

2ኛ) የአየር ንብረት ለውጥ በቡና ላይ የሚያመጣዉን ተፅዕኖ በቅርበት መከታተል፤

3ኛ) ከዚህ በፊት ቡና በማይበቅልባቸዉ ከፍታ ቦታዎች ለቡና ተክል የሚኖራችዉን ተስማሚነት ማጥናት፤

4ኛ) ለዛፎችና ለአፈር እንክብካቤ ማድረግ፤

5ኛ) የቡናን ምርታማነትና ጥራት ማሳደግ፤

6ኛ፟) ገበሬዎች ለሚሸጡት ቡና ተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኙ ማድረግ፤

7ኛ) የቡና ተክልን የአደጋ ተቋቋሚነት ለማሳደግ የሚረዱ እርምጃዎችን መዉሰድ፤ እነርሱም እርከን መሥራትን፣ የቡና ዛፍን በወቅቱ መከርክምን፣ የጥላ ዛፍ እንዲኖር ማድረግንና የመስኖ አጠቃቀምን ይመለከታል።

8ኛ) የሀገሪቱ ቡና ያለበትን ሁኔታ በወቅቱ የሚያሳውቅና ተከታታይነቱንም በበላይነት የሚያስተዳድር አካል እንዲቋቋም ማድረግ ናቸዉ።

በዚሁ አጋጣሚ የራሴን ሥጋትና የመፍትሔ ሀሳቦች ለአንባቢያን ማካፈል እወዳለሁ።

1ኛ) በሦስት ዋና የአየር ንብረት መለኪዎች (ማለትም የዝናም መጠን፣ የአየር ሙቀት እና የአየር ርጥበት) በመመርኮዝ የቀረቡት ጽሑፎች እንደሚያሳዩት የወደፊቶቹ የቡና እርሻዎቻችን የሚኖሩት ከፍ ባሉ ሥፍራዎች ላይ ነዉ። ይህ በርካታ ጥያቄዎችን ሊያመጣ ይችላል። ከነዚህ ዉስጥ የሚከተሉት ይገኙባቸዋል። የቡና ተክል ዕድገትና ምርት እንዲሁም የቡና ጣዕም ላይ ከአየር ንብረት በተጨማሪ የአፈር ዓይነትም ተፅዕኖ እንደሚያሳድር ይገመታል። የአሁኑ ጥናት ይህን አላካተተትም። ስለዚህ ወደፊት የሚደረጉ ጥናቶች የአፈሩን ዓይነትና ሌሎች ተዛማጅ ባህርያትን ማጥናት ያስፈልጋል። በአሁኑ ወቅት ከፍ ባሉ ሥፍራዎች የሚበቅሉ ሌሎች የሰብል ዓይነቶችስ ዕጣ ምን ሊሆን እንደሚችል አይታወቅም ምክንያቱም እርሻቸው በቡና የሚተካ ከሆነ ማለቴ ነዉ። ከዚህ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት ሌላ ሰብል የሚያመርቱ ገበሬዎችስ እንዴት እርሻቸዉን በቀላሉ ወደ ቡና ሊቀይሩ እንደሚችሉ ማወቅ ያስፈልጋል።

2ኛ) በአየር ንብረት ለዉጥ ምክንያት ታዋቂዉ የአረቢካ ቡናችን በአግባቡ ምርት ሊያፈራ የማይችልባቸዉ ቦታዎች ተለይተዉ ቀርበዋል። ስለዚህ ከፍተኛ የአየር ሙቀትም ሆነ ተባይና በሽታ በተሻለ ሁኔታ መቋቋም የሚችለዉን የሮቡስታ የቡና አይነት በሀገራችን የምናላምድበት መንገድ ቢፈጠር የሚል ሀሳብ አቀርባለሁ። ነገር ግን መጠነ ሰፊ የሆነ ሥራ በዚህ ለሀገራችን አዲስ በሆነ የቡና አይነት ላይ ከመጀመራችን በፊት ወካይ በሆኑ የሀገሪቷ ሥፍራዎች ጥልቅ የሆነ ምርምር ማካሄድ ያስፈልጋል። በዓለማችን የሮቡስታን ቡና በሰፊዉ ከሚያበቅሉ ሀገራትም ልምድ መዉሰድ ጠቃሚ ነዉ።

ምንም እንኳ ባብዘኛዉ የቡና ጠጪዮች ዘንድ የአረቢካ ቡና የበለጠ ተመራጭ ቢሆንም የሮቡስታ ቡናም የራሱ የሆኑ ጠንካራ ጎኖች አሉት። የሚከተሉትን መለኪያዎች ለማነጻጸሪያነት ማየት ይቻላል።

መለኪያዎች የአረቢካ ቡና የሮቡስታ ቡና
ተስማሚ ሥፍራ ከፍተኛ (እስክ 2000 ሜ) ዝቅተኛ (እስክ 1000 ሜ.)
ተስማሚ የአየር ሙቀት 15-25 ሴ.ግ. 20-30 ሴ.ግ.
የተክሉ ትልቅነት አነስ ያለ ከፍ ያለ
ተባይ የመቋቋም ችሎታው ዝቅተኛ ከፍተኛ
በሽታ የመቋቋም ችሎታው ዝቅተኛ ከፍተኛ
የምርት መጠን ዝቅተኛ ከፍተኛ
የካፊን መጠን ዝቅተኛ ከፍተኛ
ጣፋጭነት ጠፈጥ ያለ መረር ያለ

በመጨረሻም ታዋቂ የሆኑ የቡና ብራንዶቻችንን እንዳናጣና ከዘገየ ደግሞ ወደቀድሞ ሁኔታ መመለስ አዳጋች ስለሚሆን ወደ መፍትሔዉ በፍጥነት መሄድ ይኖርብናል። ለዚሁም የሁሉም የድርሻ አካላት ንቁ ተሳትፎ ያስፈልጋል።

በሚቀጥለዉ በሌላ ጽሑፍ እንገናኝ።

ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ግንቦት 22፤ 2011 ዓ.ም.

አስተያየት ያስቀምጡ