በዚህ ብሎግ ሥር ግብርናን በተመለከተ በተለያዩ ርዕሶች በተከታታይ አጫጭር ጽሁፎች አቀርባለሁ። እነዚህ ጽሑፎች የሚያተኩሩት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያለዉ ህዝባችን በሚተዳደርበትና የኔም የሙያ መስኬ በሆነዉ ግብርና ላይ የራሴን አስተዋጽዖ ለማበርከት ነዉ። የዛሬዉ እነሆ፤
የቡናችን ነገር እጅግ ያሳስባል
ክፍል አንድ
እንደሚታወቀዉ ሁሉ ቡና በዓለማችን እጅግ ተወዳጅ መጠጥ ነዉ። በዓለማችን ሁለት የቡና ዓይነቶች በሰፊዉ ይበቅላሉ፣ በገበያም ላይም ይዉላሉ። እነርሱም አራቢካ እና ሮቡስታ ተብለው ይታወቃሉ። በዓለም ላይ የአረቢካ ቡና ስልሳ ፐረሰንት በሆነ መሬት ላይ ሲተከል በተቀረዉ አርባ ፐርሰንት መሬት ላይ ደግሞ የሮቡስታ ቡና ይተከላል። የአራቢካ ቡና በሰፊዉ የሚበቅለው ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ ባሉ ሀገሮችና በመካከለኛዉና ደቡብ አሜሪካ ሀገሮች ነዉ። በሌላ በኩል የሮቡስታ ቡና በሰፊዉ የሚበቅለዉ በመካከለኛዉና ምዕራብ የአፍሪካ እና በደቡብ ምሥራቅ ባሉ የኤሲያ ሀገሮች ነው። ይህ የሚያሳየዉ እነዚህ ሁለት የቡና ዓይነቶች የሚበቅሉበት የአየር ንብረትና የአፈር ሁኔታ የተለያየ መሆኑ ነዉ። በተጠቃሚዎች ዘንድ ከሁለቱ የቡና ዓይነቶች የአራቢካ ቡና የበለጠ ተመራጭ ነዉ። ይህም በጣዕሙና ለጠጪዎች በሚሰጠዉ ዕርካታ የተነሣ ነዉ። በዚሁ መሠረት በገበያ ላይ የአረቢካ ቡና ከሮቡስታ ቡና በላይ ከፍ ያለ ዋጋ ያወጣል። ስለዚህ ለሽያጭ የቀረበዉ ቡና የአረቢካ ዓይነት ብቻ ከሆነ በፓኮዉ ላይ በፎቶዉ ላይ እንደሚታየዉ 100% አረቢካ ተብሎ ይጻፍበታል። ሸማቹም ቡናዉ ሙሉ በሙሉ የአረቢካ ቡና ከሆነ ከፍ ያለ ክፍያ ቢፈጽምም አይቆጨዉም።

ወደ ሀገራችን ስንመለስ ምንም እንኳ በሀገሪቷ በሙሉ የሚመረተዉ ቡና በተጠቃሚዎች ዘንድ ከፍተኛ ተመራጭ ያለዉ የአረቢካ ቡና ብቻ ቢሆንም ሀገሪቱ ለረጅም ጊዜ በዓለም ገበያ ተመጣጣኝ ዋጋ ልታገኝ አልቻለችም። በዚሁ መሠረት በተለያየ የሀገሪቱ ክፍል የሚመረቱትና የራሳቸዉ የሆነ ልዩ ጣዕም ያላቸዉ እንደ ይርጋጨፌ፣ ሐረር፣ ሲዳሞ የመሳሰሉት የቡና ዓይነቶች (ወይም ብራንዶች) በዉጭዉ ዓለም ዕዉቅና ተነፍጓቸዉ ቆይቶ ነበር። ሆኖም በተለምዶ የቡና ጦርነት ተብሎ በሚታወቀዉና በኢትዮጵያ መንግሥትና ዋናዉ ጽህፈት ቤቱ በአሜሪካን ሀገር በሚገኘዉ በስታርበክስ መካከል በነበረዉ ከፍተኛ አለመግባባት ኦክስፋም ተብሎ የሚጠራዉ ግብረ ሠናይ ድርጅት ከፍተኛ እግዛ ለኢትዮጵያ በማድረጉ ከላይ የተጠቀሱት የቡና ብራንዶች በአሜሪካና ሌሎቸ ሀገሮች ዕውቅና እንዲኖራቸዉ ሆኗል። በነዚሀ ሀገራት ያሉ የቡና ጠጪዎችም ከላይ የተገለጹትን የቡና ብራንዶች ለይቶ ማወቅ ብቻ ሳይሆን የሚፈልጉትን የቡና ብራንድ በገበያ ሊያገኙ ችለዋል። በዚህ መሠረት የተለያዩ የኢትዮጵያ የቡና ብራንዶች እንደ ጥራታቸዉ ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ ሊያገኙ ችለዋል።
የዛሬዉ ብሎጌ የሚያተኩረዉ በአሁኑ ወቅት በቡናችን ላይ የተደቀነበትን አሳሳቢ የተፈጥሮ ክስተት ለአንባቢያን ለማስገንዘብ ሲሆን ይህንን አደጋ ለመታደግም ሁላችንም የየራሳችንን አስተዋዖ እንድናበረክት ነዉ። የጽሑፌ መነሻ ሀሳብም በቅርብ ጊዜ በጥናት ላይ ተመርኩዘዉ የታተሙ ሁለት ጽሁፎች ሲሆኑ እነርሱም Coffee Farming and Climate Change in Ethiopia እና Resilience potential of the Ethiopian coffee sector under climate change የሚባሉት ናቸዉ። እነዚህ ሁለት ጽሑፎች ኢትዮጵያ የሚገኙ የቡና አብቃይ ሥፍራዎችን ሁሉ ባገናዘበ መልኩ የተሠሩ ዉጤቶች ናቸዉ። የጥናቱ ዋና አካላት በእንግሊዝ ሀገር የሚገኘዉና የብዝሀ ሕይወትን በመንከባከብ የሚታወቀዉ የኪዉ ጋርደንና በኢትዮጵያ ያሉ ተመራማሪዮች ናቸዉ። በኢትዮጵያ በኩል በጥናቱ ከተሳተፉት መካከል ዕዉቁ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባና የጉለሌ የዕጽዋት ጋርደን ዳይሬክተር የሆኑት ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰዉ ይገኙበታል። ፕሮፌሰር ሰብስቤ ከሌሎች ሁለት የሥራ ባልደረቦቻቸዉ ጋር በመሆን እ.ኤ.አ. ብ2010 ባሳትሙት Atlas of the potential vegetation of Ethiopia በሚባል መጽሐፍቸዉም ጭምር ይታውቃሉ። ፕሮፌሰር ሰብስቤ ሰፊ ጥናት ከማካሄዳቸዉም በተጨማሪ በመስኩ ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጾዖ ባለፈዉ ዓመት በእንግሊዝ ሀገር ከ350 ዓመታት በፊት የተቋቋመዉ የታዋቂዉ የሮያል ሶሳዪቲ አባል ለመሆን በቅተዋል። በዚህ አጋጣሚ ከላይ የተገለጹትን የቡና ጥናቶች እንዲካሄዱ በመዋዕለ ንዋይ ለረዱት ለእንግሊዝ፣ ኖርዌና ዴንማርክ መንግሥታት ምሥጋና ይገባቸዋል።
ጥናቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ የቡና አብቃይ ሥፍራዎችን እንደ ኩታ ገጠምነታቸዉ በአምስት ዋና ክፍሎች የሚከፍል ሲሆን 16 የቡና ሥፍራዎችንም ለይቶ ያቀርባል። ጥናቱም በዋናነት መሠረት ያደረገው ባለፉት 40 ዓመታት በነዚህ ቡና አብቃይ ሥፍራዎች የተከሰተዉን የአየር ንብረት ለውጥ ነዉ። የጥናቱ ዉጤት እንደሚያሳየዉ እ.ኤ.አ. ከ1960 እስከ 2006 ድረስ ባሉት 46 ዓመታት ብቻ በኢትዮጵያ የአየር ሙቀት በ1.3 ድግሪ ሴንቲ ግሬድ ከፍ ብሎ ታይቷል። ከዚህ በተጨማሪ ለቡና ዕድገት አስፈላጊ የሆኑ ቀዝቃዛ ሌሊቶች አጥረው ታይተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ጥናቱ ባካተተዉ 46 ዓመታት የበልግ ዝናም መጠን በተለይም በደቡብ ምሥራቅ ባሉ የቡና አብቃይ ሥፍራዎች ከ15 እስክ 20% አንሶ ተገኝቷል። ይህ መጠነ ሰፊ ጥናት በተለያዩ የአየር መለኪያ መሣሪያዎች ብቻ የተመረኮዘ ሳይሆን ለአራት ዓመታት በርካታ ቁጥር ያላቸዉ በተለያዩ የቡና አብቃይ ሥፍራዎች የሚገኙ ገበሬዎችንም በማነጋገር ነበር። ከገበሬዎች ቃለ ምልልስ የተገኘዉ ውጤት ከአየር መለኪያ መሣሪዎች ከተገኘዉ ጋር ተመሣሣይነት አለዉ። ገበሬዎቹ የአየር ንብረት ለውጥ በቡና ተክላቸዉም ሆነ ምርታቸዉ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳደረባቸው ከተገነዘቡ ቆይቷል። ይህ መጥፎ የተፈጥሮ ክስተት ከመምጣቱ በፊት በየዓመቱ ምርት ያገኙ የነበረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን አንድ ደህና ምርት በየሁለት ዓመት ወይም ባንዳንድ ሥፍራዎች በየአምስት ዓመት ብቻ ማግኘት ከጀመሩ ሰንበትበት ብሏል።
በአጠቃላይ እነዚህ ጽሁፎች በሀገሪቱ ያሉ የቡና አብቃይ ሥፍራዎች በአሁን ወቅት የገጠማቸዉን የአየር ንብረት ለውጥ ከማሳወቃቸዉም በላይ በሚቀጥሉት አሥርት ዓመታትም ሊያጋጥማቸዉ ይችላል ተብሎ የሚገመተዉን በሣይንሳዊ መንገድ መተንተናቸዉ ነው። በነዚህ ጥናቶች መሠረት ከዚህ በፊት የቡና አብቃይ ከነበሩትሥፍራዎች መካከል በምዕራብና ምሥራቅ ሐረርጌ፣ በአርሲና በዘጌ ያሉ ቦታዎች በአሁኑ ወቅት ለቡና ተክል ተስማሚ ሆነዉ አልተገኙም። ወደፊትም ወደ ቀድሞ የአምራችነታቸዉ ሁኔታ የመመለስ ዕድላቸዉ የመነመነ ነዉ። በጥናቱ መሠረት እስከሚቀጥሉት 20 ዓመታት ደግሞ በባሌ ያሉ መሬቶችም ለቡና እርሻ ተስማሚ አይሆኑም። ከዚያም ቀጥሎ ባሉት ከ20 እስክ 50 ዓመታት ደግም ከስምጥ ሸለቆ ሰሜን ያሉ ሥፍራዎች ቡናን የማያበቅሉ ሲሆን የትንበያው መጨረሻ በሆነዉ ከ50 እስከ 80 ዓመታት ባሉት ጊዜያት ደግሞ ከስምጥ ሸለቆ ደቡብ ያሉ ሥፍራዎችም ተመሣሣይ ዕድል ይገጥማቸዋል። ምንም እንኳ በምዕራብ የሀገሪቱ ክፍል ያሉ የቡና አብቃይ ሥፍራዎች እስከሚቀትሉት 80 ዓመታት ቡናን በማብቀል እንደሚቆዩ ቢገመትም ባንዳንድ ሥፍራዎች የተስማሚነት ደረጃቸዉ እንደሚቀንስ ይጠበቃል። ይህ በኢትዮጵያም ሆነ በሌላ ዓለም ለሚገኙ የቡና አፍቃሪዎች አስደንጋጭ ዜና ነዉ። በያመቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በቡና ለምታገኘዉ ሀገራችንም ጭምር።
ስለዚህ ቡናችን እያየነው እንዳይጠፋብን ካሁኑ ሁላችንም የድርሻችንን ማበርከት ይኖርብናል። ከዘገየ ወደ ቀድሞ ሁኔታ መመለስ አስቸጋሪ ብቻ ሳይሆን ፈጽሞ ላይሆንም ይችላል። ከላይ በጥናት ላይ ተደግፎ የቀረበዉን በተለይ የሐረር እና የባሌ የቡና ዓይነቶች ላይ የተደቀነዉን ሳነብ ከረጅም ዓመታት በፊት የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ‘‘ቡና’’ ተብሎ በሚጠራዉ ኮርስ መምህራችን የነበሩት ታዋቂዉ የጅማ እርሻ ምርምር የቡና ተመራማሪ ዶክተር መስፍን አምሐ ትዝ አሉኝ። በዚህ አጋጣሚ ማስገንዘብ የምፈልገዉ የሐረር ቡና ተብሎ የሚታወቀዉ የቡና ብራንድ በምሥራቅና ምዕራብ ሐረርጌ አካባቢዎች የሚመረተዉን የቡና ዓይነት የሚወክል ነዉ። እኚሁ መምህር በክፍል ዉስጥ ይሰጡ ከነበረዉ ሌክቸር በተጨማሪ ባንድ ውቅት ድሬዳዋ ከተማ ውስጥ ወደሚገኝ የቡና ማቀነባበሪያ ለጉብኝት ወስደዉን ነበር። ይህ መለስተኛ ማቀነባበሪያ ቡናን በመቁላትና በማሸግ በተለይም የሐረርን ቡና ለውጭ ሀገር ገበያ በሚቀርብበት መንገድ የሚያዘጋጅ ነበር። የሐረር ቡና የሚታወቅበት የራሱ የሆነ ልዩ ጣዕም ያለዉ ሲሆን ይህም ወደ ጣፋጭነት የሚያደላ ነዉ። በዚሁ ጣዕሙ የተነሣ በመካከለኛዉ ምሥራቅ ባሉ ሀገራት ዘንድ ተወዳጅነት ያተረፈ ነበር። ታዲያ እንደዚህ ታዋቂ የሆነዉን የሐረርና ሌሎችም የቡና ዓይነቶኛችን ልናጣ ነዉን? ምንስ ይበጀናል? ወደ ተግባርም በፍጥነት ልንሄድ አይገባንምን?
የጥናቱ ተሣታፊዎች በርካታ መደረግ የሚገባቸዉን ምክር ለግሰዋል። እነዚህና ሌሎች የመፍትሔ ሀሳቦች በሚቀጥለዉ ጽሑፌ አቀርባለሁ።
ዘሪሁን ታደለ፣ ከበርን ከተማ ስዊዘርላንድ፣ ግንቦት 18፤ 2011 ዓ.ም.